በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
አንድ ቀን ቅዱስ እንጦንስ (የመነኮሳት ሁሉ አባት) እንዲህ ሲል አሰበ:: "በውኑ በበርሃ ለበርካታ ዘመናት በመኖር ከእኔ የሚቀድም (የሚበልጥ) ሰው ይኖር ይሆን?" ይህንን ሃሳቡን ገና ሳይጨርሰው ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ ዘንድ ደረሰ::
"እንጦንስ ሆይ! ከእኔ የሚቀድም የበርሃ ሰው ይኖር ይሆን ብለህ አስበሃል::
በእርግጥም ከአንተ 20 ዓመታትን ቀድሞ ወደ በርሃ የገባ በቅድስናው ፈጣሪውን ያስደሰተ ዓለም ከነ ክብሯ የእግሩን መረገጫ ያህል እንኩዋ የማትመጥነው በጸሎቱና በምልጇው ዓለም የምትጠበቅለት ሞገስን የተሞላ አንድ ሰው በበርሃ ስላለ ሒድና ተመልከተው" ብሎት ተሠወረው::
ቅዱስ እንጦንስም ከሰማው ነገር የተነሳ እየተደነቀ ተነሳ:: እርሱ ካለበት በርሃ በራቀ መንገድም ለቀናት ተጉዞ አንድ በዓት (ዋሻ) በር ላይ ደረሰ:: በበሩ አካባቢ የሰውና የአራዊት ኮቴ ተመልክቶ በሩን ጸፋ (ቆፈቆፈ)::
በውስጥ ያለው አረጋዊ ሰው ግን ትልቅ ድንጋይ ገልብጦ በሩን አጠበቀው:: ለ80 ዓመታት ሰውን አይቶ አያውቅምና ሰይጣን ሊያታልለኝ መጥቷል ብሎ አስቧል:: ቅዱስ እንጦንስ ግን "ኃሠሥኩ እርከብ: ጐድጐድኩ ይትረኃው ሊተ (ማለትም ሽቻለሁና ላግኝ: ደጅ መትቻለሁና ይከፈትልኝ)" ሲል አሰምቶ ተናገረ::
ቅዱሱ ገዳማዊም ሰው መሆኑን ሲያውቅ በሩን ከፈተለትና ወደ ዋሻው አስገባው:: መንፈሳዊ ሰላምታንም ተለዋወጡ:: ሲመሽም ቅዱስ እንጦንስ ሽማግሌውን ገዳማዊ "ስምህ ማን ነው?" ቢለው "ስሜን ካላወክ ለምን መጣህ?" ሲል መለሰለት::
ያን ጊዜ ቅዱስ እንጦንስ ቀና ብሎ ሰማይን ሲመለከት ምሥጢር ተገለጠለትና "ቅዱስ ዻውሊ ሆይ! ከአንተ ጋር ያገናኘኝ ፈጣሪ ይክበር: ይመስገን" ሲል ፈጣሪውን ባረከ:: ቅዱስ ዻውሊም መልሶ (በጸጋ አውቆት) "አባ እንጦንስ ሆይ! እንኩዋን ደህና መጣህ" አለው:: 2ቱም ደስ ብሏቸው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ተጨዋወቱ::
" ቅዱስ ዻውሊ ማን ነው? "+
ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ዓይነት የቅድስና ሕይወት የመጀመሪያ የምትላቸው አላት:: ለምሳሌ:-
*የመጀመሪያው ሐዋርያ ቅዱስ እንድርያስ
*የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
*የመጀመሪያው መነኮስ ቅዱስ እንጦንስን እና
*የመጀመሪያውን ባሕታዊ (ገዳማዊ) ቅዱስ ዻውሊን ማንሳት እንችላለን::
ቅዱስ ዻውሊ የተወለደው በሰሜናዊ ግብጽ: በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው:: ወላጆቹ ባለጸጐች ነበሩ:: ቅዱሱንና ታላቅ ወንድሙን አባ ዼጥሮስን ወልደዋል:: 2ቱ ክርስቲያን ወንድማማቾች ገና ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው:: ሃዘናቸውን ፈጽመው ሃብት ሲካፈሉ ግን መስማማት አልቻሉም:: ምክንያቱ ደግሞ ትልቁ ዼጥሮስ ደህና ደህናውን እቃ ወስዶ መናኛ መናኛውን ለትንሹ ለዻውሎስ (ዻውሊ) መስጠቱ ነበር:: ስለዚህ ነገር ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት ሲሔዱ ግን መንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሙቶ ደረሱ::
ቆመው ሳሉም ቅዱስ መልአክ ሰው መስሎ ዻውሊን "ይህ ሰው ባለጸጋ ነው:: በገንዘቡ የሰጠውን ፈጣሪ ሲበድልበት ኑሮ እነሆ ተሸኘ:: በሰማይም አስጨናቂ ፍርድ ይጠብቀዋል" ሲል ነገረው::
በዚያች ቅጽበት የወጣቱ ዻውሊ ሐሳብ ተለወጠ:: ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ! ሁሉ ንብረት ያንተ ይሁን" ብሎት ከአካባቢው ጠፋ:: በመቃብር ሥፍራ ለ3 ቀናት ያለ ምግብ ጸልዮ የእግዚአብሔር መልአክ ሰው ወደ ማይደርስበት በርሃ ወሰደው:: በዚያም ምንጭ ፈለቀችለት:: እየጾመ ይጸልይ: ይሰግድ ገባ:: ሁሌ ማታ ግማሽ ሕብስት ከሰማይ እየወረደለት: ቅዳሜና እሑድ መላእክት እያቆረቡት ለ80 ዓመታት ኖረ:: (አንዳንድ ምንጮች ግን ለ90 ዓመታት ይላሉ) ከቅዱስ እንጦንስ ጋር የተገናኙትም ከዚህ በሁዋላ ነው::
ከቅዱስ እንጦንስ ጋር በነበራቸው የ2 ቀናት ቆይታም ቅዱስ ዻውሊ ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል:: በዚህች ቀን ሲያርፍም መቃብሩን አናብስቱ ቆፍረዋል:: ቅዱስ እንጦንስም በክብር ቀብሮታል:: 80 ዓመት የለበሳት የዘንባባ ልብሱም ሙት አስነስታለች::
<< ጻድቅ: ቡሩክ: ቀዳሚው ገዳማዊ: መላእትን የመሰለና የባሕታውያን ሁሉ አባት ለተባለ ለቅዱስ ዻውሊ ክብር ይገባል >>
"+ ገዳማዊ ሕይወት +"+
በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::
ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::
ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::
+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::
ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል:: ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::
ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ:: እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::
አምላክ በበረከታቸው ይባርከን::
"የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ::" (ዕብ. 11:35-38)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር