Saturday, May 9, 2015

ቤተክርስቲያን በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል በመሆኗ መከፈል የለባትም፤ መቼም መች አንዲት ናት። «ወንድሞቻችን በአንድ ቃል እንድትናገሩ እንድታዝኑ ፍጹማንም እንድትሆኑ ሁላችሁንም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ አሳብ ሆናችሁ ኑሩ። ወንድሞቻችን ሆይ እንደምትጣሉና እንደምትከራከሩ ከቀሎኤስ ወገኖች ስለ እናንተ ነገሩኝ። እነሆ እርስ በርሳችሁ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔ የክርስቶስ ነኝ፥ የምትሉትን እነግራችኋለሁ። ክርስቶስ ተከፍሏልን?» እንዳለ። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲። እንዳለ ቤተክርስቲያን የሁሉ ናት። በመሆኗም በዘር፥ በቋንቋ፥ በአካባቢ አትከፈልም። «በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናልና። በክርስቶስ የተጠመቃችሁ እናንተማ ክርስቶስን ለብሳችኋል፦ (መስላችኋል)። በዚህም አይሁዳዊ ወይም አረማዊ የለም፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁ።» እንዳለ። ገላ ፫፥፳፮። ቤተክርስቲያን በሰማይም በምድርም ያለች ናት። በምድር በሕይወተ ሥጋ ከከሐድያን፥ ከመናፍቃን፥ ከፍትወታት እኩያትና ፥ ከኃጣውእ ጋር የሚያጋድሉ፦ በአጸደ ነፍስ ደግሞ ተጋድሏቸውን ፈጽመው የጽድቅና የድል አክሊል ተቀዳጅተው የሚኖሩ ምእመናን አንድነት ናት። ራእ ፭፥፱-፲፪።

No comments:

Post a Comment